የሲዳማ ብሔር ታሪክና የሚዲያ እድገት

የሲዳማ ብሔር በአሁኑ የሲዳማ መሬት ሰፍሮ ኑሮውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን በምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ዘመቻዎች በኢትዮጵያ ሕዝቦች ግዛት ስር እስከ ተጠቃለለበት ድረስ የራሱና የማንነቱ መገለጫ የሆኑ ማሕበራዊ ተቋማት የነበሩትና እነዚህ ተቋማት ዛሬም ድረስ የሚገኙ ናቸው (የሲዳማ ብሔር ታሪክና ባህል፣ 2003)።

የሲዳማ ብሔር ከነባር ባህላዊ እሴቶቹ አንዱ የሆነው ነባር የኮሙኒኬሽን ስርአት (Falk Media) ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ለመላው ማህበረሰብ መረጃ ተደራሽ የሚያደርግበት ስርአት አለው፡፡ የብሔሩ የመረጃ ልዉዉጥ ስርዓት እንደዘመናዊ የመረጃ ልዉዉጥ ስርዓት በአንድ ማዕከል፤ በአጭር ጊዜ በቅርብም ሆነ በሩቅ ላሉ በርካታ ሰዎች ከአንድ ማሰራጫ ጣቢያ የተለያዩ መልዕክቶች የሚተላለፉበት እንኳን ባይሆን፤ ለረዥም ዘመናት ለግለሰብም ሆነ ለቡድን መረጃ የሚያስተላልፍበት ስርዓቶች አሉት፡፡

ከእነዚህ መካከል ዋሬ (Waare)፣ በጉዱማሌ መሰብሰቢያ፣ በመንገድ ጉዞ (በእግር) ላይ፣ በገበያ፣ በድግስ ቦታዎች፣ በለቅሶ ቦታዎችና የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች የሚከወኑበት ስፍራዎችና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሲዳማ ከዘመናዊ ሚዲያ ስርጭት አገልግሎት ጋር የተዋወቀው በ1974 ዓ.ም ከሱማሊያ በሲዳሙ አፎ መሰራጨት በጀመረው የሬዲዮ ስርጭት ነው፡፡ ስርጭቱ በሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) አማካኝነት ይሰራጭ ነበረ፡፡

ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ ቀዳሚ እንደ ሆነ የሚነገረውና እ.ኢ.አ በ1989 ዓ.ም የተቋቋመው የሲዳማ ትምህርት በሬዲዮ ማሰራጫ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በ2001 ዓ.ም የተቋቋመውና በባንሳ ከተማ የሚገኘው የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ፣ በፋና ብሮካስቲንግ ኮርፖሬት በሻሸመኔ የሲዳሙ አፎ ዜናና ፕሮግራም ስርጭት የጀመረው ኤፍኤም 103.4 የሬዲዮ ጣቢያ፣ በ2007 ዓ.ም በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሲዳሙ አፎ ዜናና ፕሮግራሞችን በማሰራጨት የጀመረው የሲዳማ ቴሌቪዥን ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ በሲዳሙ አፎ ዜናና ፕሮግራም እንዲሁም በአማርኛ ፕሮግራሞችን የሚያሰራጨው የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ (SMN) የቴሌቪዥን ማሰራጫና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሲዳሙ አፎ የሚታተመው “ባካልቻ” ጋዜጣ ይጠቀሳል፡፡

ከላይ የተገለፁ የብዙኃን መገናኛ አይነቶች በክልሉ የሚዲያ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የሚዲያ ተቋማት በተለያዩ ችግሮች የተተበተቡ ናቸው፡፡ በአደረጃጀት የስራ አመራር ቦርዶቻቸው የፈረሱባቸው፣ የተለያየ የደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የሚተገበርባቸው፣ በተለያየ የአደረጃጀት፣ የሰው ኃይልና አሰራር ችግሮች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

በነዚህ ችግሮች ውስጥም ሆነው ባላቸው የሰው ኃይልና አመራር የክልሉን ህዝብ የሚዲያ አገልግሎት በሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን ተደራሽ ለማድረግ የበኩላቸውን በመወጣት ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የተቋማቱን የሰው ኃይል እና የሚዲያ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በማሰባሰብ፣ አደረጃጀት በመፍጠርና አሰራር በመዘርጋት የክልሉን ሚዲያ ለማደራጀት የሚያስችል መነሻ አቅም ሆነው ማገልገል እንደሚችሉ ይታመናል፡፡

Copyright ©2025 SBC. All Rights Reserved ; Developered by SITA team