የኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጵያን ያስተሣሠረ ጠንካራ ገመድ ነው” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጵያን ያስተሣሠረ ጠንካራ ገመድ ነው” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሀገር ግንባታ ጋር ያለውን ጥልቅ ቁርኝት በታሪካዊ ማሳያዎች እየጠቀሱ በስፋት አብራርተዋል።  


“የኦሮሞ ሕዝብ ኢትዮጵያን ያስተሣሠረ ጠንካራ ገመድ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ትሥሥር ውስጥ ያለውን አስተዋፅኦ በማሳያዎች ዘርዝረዋል።


በ1512 ዓ.ም የባሕረ ነጋሽ ንጉሥ የነበረው 'ዶሪ' ኦሮሞ እንደነበር፣ በተጨማሪም 'ባሬንቱ' የተሰኘው ትልቅ ከተማ እና እንደ አምባ ሶይራና አምባ ደብራ ያሉ ተራራዎች ስያሜያቸው የኦሮሞ ሥረ-መሠረት እንዳለው አስረድተዋል።


የዛግዌ ሥርወ-መንግሥት እና የገዳ ሥርዓት ትሥሥር፡ የዛግዌ ሥርዓት የመጀመሪያው ንጉሥ 'መረሪ' የተባለ የኦሮሞ ስም ያለው መሆኑን፣ እንዲሁም ነገሥታቱ (እንደ ይምርሃና እና ላሊበላ ያሉት) ለ40 ዓመታት መግዛታቸው በገዳ ሥርዓት (8x5=40) ሥልጣን ከሚረከብበት ዕድሜ ጋር ያለውን አስገራሚ መመሳሰል ጠቁመዋል። አሁንም ድረስ በላሊበላ ዙሪያ አፋን ኦሮሞ የሚናገሩ ማኅበረሰቦች መኖራቸውንም አክለዋል።


የሥነ-ሕንፃ እና የቅርሶች መመሳሰል፦ በአክሱም እና በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ያለው የባህል መገለጫ (የአለባበስ) መመሳሰል፣ እንዲሁም በባሌ የሚገኘው የሶፍ ዑመር ዋሻ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ካሉ ዋሻዎች ጋር ያለው መመሳሰል፣ እንዲሁም በላሊበላ የሚገኘው ውቅር ቤተ-ክርስቲያን (ቤተ ጊዮርጊስ) በሸዋ ከሚገኘው አዳዲ ማርያም ጋር ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው በመውጣት በአሠራርም ሆነ በዘመን ያላቸውን ጥልቅ ተመሳሳይነት አንሥተዋል። 


የዘመኑ ማኅበረሰቦች ዘመናዊ መጓጓዣ ባልነበረበት ወቅት የነበራቸውን ጥልቅ የታሪክ እና የምሕንድስና ትሥሥርን እንደሚያሳይ አብራርተዋል። 


ማኅበራዊ መስተጋብር በጎጃም፦ በጎጃም አካባቢ "ቄሮ ገብርኤል" የሚባል የኦሮሞ ስያሜ ያለው መንደር መኖሩ በ16ኛው ክፍለ ዘመን እና ከዚያም በፊት በሕዝቦች መካከል የነበረውን ሰፊ መስተጋብር ያሳያል።


የዘመናዊው ትግል አቃፊነት፦ የመጫ እና ቱለማ ማኅበር ሲመሠረት ትግሉ የኦሮሞን ሕዝብ መብት ከማስከበር ባለፈ የሌሎችንም ብሔር ብሔረሰቦች (እንደ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ አፋር፣ ሶማሌ ወዘተ) ጥያቄ ያቀፈ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። 


በተለይም የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም መምጣቱን ተከትሎ ትግሉ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መልክ በመያዝ አቃፊነቱን አስመስክሯል ነው ያሉት። (ኢቢሲ)


አስተያየትዎን ያጋሩ
ቋንቋ ይቀይሩ
ፍለጋ
ወቅታዊ ዜናዎች
የስራ ማስታወቂያ
SBC
የፌስቡክ ገጽ
ዩቲዩብ