የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል

የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል

የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል


‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ 

ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት››


«ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፤ 

ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ»


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዓበይት በዓላት መካከል የሚጠቀሰው የደብረ ታቦር በዓል በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን ይከበራል።


ደብረ ታቦር ጌታችን ከሦስቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ተራራ ወጥቶ፣ መልኩ እንደ ፀሐይ የበራበትና ልብሱም እንደ ብርሃን የነጣበት፣ ብርሃነ መለኮቱንም የገለጠበት ክስተት ነው።


ቡሄ” የሚለው ቃል መላጣ፣ ገላጣ፣ ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅና የተገለጠ የሚል ትርጉም ይይዛል። በኢትዮጵያ ክረምቱ፣ ጭጋጉና ደመናው እየተራገፈ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት ወቅት ከበዓሉ ጋር በመገጣጠሙም በዓሉ “ቡሄ” ተብሎ መጠራቱ ይነገራል።


ቡሄ ሲደርስ ክረምቱ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከጭጋግ ወደ ጥራት እንደሚሸጋገር ይታመናል። ይህንንም አባቶቻችን፣ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” በሚለው ተረት አጠናክረው አስተላልፈውታል።


ስለዚህ በቡሄ በዓል የሚታየው ችቦ የብርሃን ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ የደብረ ታቦርን ብርሃናዊ ምስጢር የሚያስታውስ ነው።


የቡሄ ዋዜማ ሲደርስ ሕፃናት ከቤት ወደ ቤት እየዞሩ “ቡሄ በሉ፤ ቡሄ በሉ” እያሉ ይጫወታሉ። እናቶችም የተዘጋጀውን የቡሄ ዳቦ ለልጆች ይሰጣሉ።


ለኢትዮጵያውያን ቡሄ ባህላዊ ደስታ ብቻ ሳይሆን፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮት የተገለጠበትን የደብረ ታቦር በዓል የሚያስታውስ መንፈሳዊ ትውፊትም ነው።


ጅራፍ ደግሞ የቡሄ ልዩ መገለጫ ነው። ሕፃናት ከበዓሉ ቀደም ብለው ጅራፍ ይገምዳሉ፤ በበዓሉም ይገርፋሉ። የጅራፉ ጩኸት ከድምፀ መለኮት ጋር የተያያዘ ምሳሌያዊ ትርጉም እንዳለው ይነገራል ።


በዘመናዊ አኗኗር ምክንያት አንዳንድ ቦታዎች የቡሄ መንፈሳዊ ይዘት እየተዳከመ እየመጣ ነው። የበዓሉን ትርጉም ሳያውቁ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ የሚዘዋወሩ ልጆች፣ የመንፈሳዊ ዜማዎች መቀነስና ከበዓሉ መንፈስ የራቁ አከባበሮችም ይስተዋላሉ።


ስለዚህ ወላጆች፣ መምህራንና ምእመናን ለቀጣዩ ትውልድ የቡሄን ታሪክ፣ የደብረ ታቦርን መንፈሳዊ ትርጉምና የበዓሉን ትውፊት ማስተላለፍ ይገባቸዋል።


ቡሄ የቀን መለወጥ ብቻ አይደለም፤ ብርሃንን የሚያስታውስ፣ የደብረ ታቦርን ምስጢር የሚያወሳ፣ ትውፊትን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚያስተላልፍ የእምነትና የባህል ውርስ ነው።


መልካም የቡሄ በዓል!


ቆንጅት አየለ


አስተያየትዎን ያጋሩ
ቋንቋ ይቀይሩ
ፍለጋ
ወቅታዊ ዜናዎች
የስራ ማስታወቂያ
SBC
የፌስቡክ ገጽ
ዩቲዩብ