ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተላለፈ የጥንቃቄ ማሳሰቢያ

ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የተላለፈ የጥንቃቄ ማሳሰቢያ
አሁን በምንገኝበት የክረምት ወቅት ሀዋሳን ጨምሮ በዙሪያዋ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ እየጣለ ይገኛል። የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ባለስልጣን በሰጠው መረጃ መሠረትም የዝናቡ መጠን በቀጣዮቹ ቀናት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ተገልጿል።
​በዛሬው ዕለት በከተማችን የጣለው ከባድ ዝናብ፣ በረዶና ኃይለኛ ንፋስ በአንዳንድ አካባቢዎች ዛፎችንና የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በመጣሉ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አስከትሏል። በተጨማሪም በመሠረተ ልማት ላይ በደረሰ ውድመት ምክንያት በአንዳንድ የከተማዋ ክፍሎች የመብራት አገልግሎት ተቋርጧል።
​የከተማ አስተዳደሩ በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፤ በተጎዱ አካባቢዎች ፈጥኖ በመድረስ ተጎጂዎችን ወደ ሕክምና የማድረስና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በመለየት ተገቢውን ድጋፍ የማድረግ ሥራዎችን አስጀምሯል።
​በቀጣይም የክረምቱ ወቅት እስኪያልቅ ድረስ መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ፣ ጉዳቱን ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ተጠናክረው እየተከናወኑ ይገኛሉ።
​በመሆኑም በቀጣዮቹ ቀናት ኃይለኛ ንፋስ የታጀበ ዝናብና የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስተዳደሩ ያሳስባል።
​በተለይም ዛፎች፣ ያረጁ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች እና አጥሮች ሊወድቁ ስለሚችሉ፣ በዝናብ ወቅት ከእነዚህ አካባቢዎች በመራቅ ራሳችሁንና ቤተሰቦቻችሁን እንድትጠብቁ ጥሪ ያቀርባል።
​በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት የቅድመ መከላከል ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ የከፋ አደጋ እንዳይደርስ የሚያስፈልጉ እርምጃዎችን ሁሉ እየወሰደ መሆኑን ይገልፃል።
የሀዋሳ ከተማ ኮሙኒኬሽን


አስተያየትዎን ያጋሩ
ቋንቋ ይቀይሩ
ፍለጋ
ወቅታዊ ዜናዎች
የስራ ማስታወቂያ
SBC
የፌስቡክ ገጽ
ዩቲዩብ